ስለ ዘካህተል ፊጥር ምንህያል እናቃንለን

ዘካህ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

2፥277 እነዚያ ያመኑ፣ መልካም ሥራዎችንም የሠሩ፣ ሶላትንም ያስተካከሉ፣ *”ዘካንም የሰጡ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም”*፡፡ إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَآتَوُا الزَّكَاةَ لَهُمْ أَجْرُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ وَلَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ 

“ኢሥላም” إِسْلَٰم የሚለው ቃል “አሥለመ” أَسْلَمَ ማለትም “ታዘዘ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “መታዘዝ” ማለት ነው። “አርካን” أَرْكان‎ ማለት “ምሰሶ” ማለት ነው፥ “አርካኑል ኢሥላም” أَرْكان‎ إِسْلَٰم ማለት “የኢሥላም ምሰሶ” ማለት ነው። የኢሥላም ምሰሶ ደግሞ አምስት ናቸው፥ እነርሱም፦ ሸሃደተይን፣ ሶላት፣ ዘካህ፣ ሰውም እና ሐጅ ናቸው፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 40, ሐዲስ 4
ኢብኑ ዑመር እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”ኢሥላም በአምስቱ መሠረቶች ላይ ተገንብቷል፤ እነርሱም፦ “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም፥ ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ ነው” በሚል ምስክርነት፣ ሶላትን በመቆም፣ ዘካህን በመስጠት፣ ረመዷንን በመፆም እና የአላህ ቤት በመጎብኘት”*። عَنِ ابْنِ عُمَرَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ بُنِيَ الإِسْلاَمُ عَلَى خَمْسٍ شَهَادَةُ أَنْ لاَ إِلَهَ إِلاَّ اللَّهُ وَأَنَّ مُحَمَّدًا رَسُولُ اللَّهِ وَإِقَامُ الصَّلاَةِ وَإِيتَاءُ الزَّكَاةِ وَصَوْمُ رَمَضَانَ وَحَجُّ الْبَيْتِ

“ዘካህ” زَكَوٰة የሚለው ቃል “ዘካ” زَكَىٰ ማለትም “ጠራ” ከሚል የግስ መደብ የመጣ ሲሆን “መጥራራት” ማለት ነው፦
20፥76 ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ አሏቸው፡፡ *ይህም “የተጥራራ” ሰው ምንዳ ነው*፡፡ جَنَّاتُ عَدْنٍ تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا ۚ وَذَٰلِكَ جَزَاءُ مَن تَزَكَّىٰ 

“የተጥራራ” ለሚለው ግስ የገባው ቃል “ተዘካ” تَزَكَّىٰ ሲሆን የስም መደሙ “ዘካህ” زَكَوٰة ነው። ይህ ቋንቋዊ ፍቺው ሲሆን ሃይማኖታዊ ፍቺው ደግሞ “ዘካህ” ማለት “የግዴታ ምጽዋት” ማለት ነው፥ አምላካችን አላህ ከሰጠን ሲሳይ ላይ የምንለግሰው ልግስና ዘካህ ይባላል፦
2፥277 እነዚያ ያመኑ፣ መልካም ሥራዎችንም የሠሩ፣ ሶላትንም ያስተካከሉ፣ *”ዘካንም የሰጡ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም”*፡፡ إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَآتَوُا الزَّكَاةَ لَهُمْ أَجْرُهُمْ عِندَ رَبِّهِمْ وَلَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ 
8፥3 እነዚያ ሶላትን ደንቡን አሟልተው የሚሰግዱ *”ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚለግሱ ናቸው”*፡፡ الَّذِينَ يُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَمِمَّا رَزَقْنَاهُمْ يُنفِقُون

ዘካን የሚሰጡ አላህ ዘንድ ምንዳ አላቸው፥ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም። “ሪዝቅ” رِزْق ማለት “ሲሳይ” ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ ደግሞ “አር-ረዛቅ” الرَّزَّاق ማለትም “ሲሳይን ሰጪ” ነው። “ኢንፋቅ” إِنفَاق ማለት “ልግስና” ማለት ሲሆን “ሙንፊቂን” مُنفِقِين ደግሞ “ለጋሾች” ማለት ነው። አምላካችን አላህ ከሰጠን ሲሳይ የምለግሰው ልግስና የበረከት ምንጭና ለአላህ ውዴታ ያለን መገለጫ ነው። ዘካህ መስጠት በረከትን ያፋፋል፥ ነገር ግን መስጠት ያለብን የአላህን ውዴታ ለመሻት እንጂ ትርፍ ፈልገን መሆን የበትም፦ 
2፥276 *”አላህ አራጣን በረከቱን ያጠፋል፡፡ ምጽዋቶችንም ያፋፋል”*፡፡ አላህም ኃጠኢተኛ ከሓዲን ሁሉ አይወድም፡፡ يَمْحَقُ اللَّهُ الرِّبَا وَيُرْبِي الصَّدَقَاتِ ۗ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ كُلَّ كَفَّارٍ أَثِيمٍ 
30፥39 *”ከበረከትም በሰዎች ገንዘቦች ውስጥ ይጨመር ዘንድ የምትሰጡት አላህ ዘንድ አይጨምርም፡፡ ከምጽዋትም የአላህን ፊት የምትሹ ሆናችሁ የምትሰጡት እነዚያ ሰጪዎች አበርካቾች እነርሱ ናቸው”*፡፡ وَمَا آتَيْتُم مِّن رِّبًا لِّيَرْبُوَ فِي أَمْوَالِ النَّاسِ فَلَا يَرْبُو عِندَ اللَّهِ ۖ وَمَا آتَيْتُم مِّن زَكَاةٍ تُرِيدُونَ وَجْهَ اللَّهِ فَأُولَـٰئِكَ هُمُ الْمُضْعِفُونَ 

ዘካህ ከጥንት ጀምሮ ነቢያት እስካሉ ድረስ የነበረ ከኢሥላም ምሰሶ አንዱ ነው፥ አላህ ዘካንም ስለ መስጠት ትእዛዝ ከነቢያችን”ﷺ” በፊት ወደ ነበሩት ነቢያት አውርዷል፦
21፥73 *”ወደ እነርሱም መልካም ሥራዎችን መሥራትን፣ ሶላትንም መስገድን፣ ዘካንም መስጠትን አወረድን”*፡፡ وَأَوْحَيْنَآ إِلَيْهِمْ فِعْلَ ٱلْخَيْرَٰتِ وَإِقَامَ ٱلصَّلَوٰةِ وَإِيتَآءَ ٱلزَّكَوٰة

ስለዚህ የኢሥላም ማዕዘን የሆነው ዘካህ ኢሥላም እስካለ ድረስ ከጥንት ጀምሮ አለ ማለት ነው። ዘካህ ከነቢያችን”ﷺ” በፊት በነበሩት ነቢያት ጊዜ ከመቶ 2.5 % ላይሰጥ ይችል ይሆናል፥ ወይ ያንሳል አሊያም ይበዛ ይሆናል። ምናልባት ከመቶ 10 % አሥራት ሊሆን ይችል ይሆናል፥ ወሏሁ አዕለም። 
በነቢያችን”ﷺ” ሸሪዓህ ግን ዘካህ ከካፒታል ላይ ከመቶ 2.5 % የሚሰጥ ነው፥ ነቢያችን”ﷺ” ከሁለት መቶ ዲርሀም 5% ዘካህ እንደሚወጣ ተናግረዋል። ያ ማለት የዘካህ ሒሳብ በመቶ ዲርሀም 5፥2=2.5 ይሆናል፦
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 9, ሐዲስ 18 ዐሊይ”ረ.ዐ” እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”ሁለት መቶ ዲርሀም ለአንተ በሆነች ጊዜና ዓመት ከሞላች አምስት ደራሂም ይወጣል፥ በአንተ ምንም ነገር አይሆንም ሃያ ዲናር እስኪሆን ድረስ”*። عَنْ عَلِيٍّ، – رضى الله عنه – عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم بِبَعْضِ أَوَّلِ هَذَا الْحَدِيثِ قَالَ ‏”‏ فَإِذَا كَانَتْ لَكَ مِائَتَا دِرْهَمٍ وَحَالَ عَلَيْهَا الْحَوْلُ فَفِيهَا خَمْسَةُ دَرَاهِمَ وَلَيْسَ عَلَيْكَ شَىْءٌ – يَعْنِي فِي الذَّهَبِ – حَتَّى يَكُونَ لَكَ عِشْرُونَ دِينَارًا

በዚህ ሐዲስ መሠረት የአንድ ሰው ካፒታል 20 ዲናር ወይም 200 ዲርሀም ሲሆን ዘካህ ይወጅበታል፥ በሸሪዓህ የዘካህ አነስተኛ የክፍያ መጠን “ኒሷብ” نِصاب ይባላል፥ ይህም ኒሷብ የሚለካው 20 ዲናር ወይም 200 ዲርሀም ሲሆን ነው። “ዲናር” دِينَار‎ ማለት “የወርቅ ሳንቲም”gold coin” ማለት ሲሆን “ዲርሀም” دِرْهَم‎ ማለት ደግሞ “የብር ሳንቲም”silver coin” ማለት ነው። 
“ዲናር” እና “ዲርሀም” የሚለኩት በሚስቃል ነው፥ “ሚስቃል” مِثْقَال የሚለው ቃል “ሰቀለ” ثَقَلَ ማለትም “ከበደ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ክብደት” ማለት ነው። 
1 ሚስቃል ወርቅ 4.25 ግራም ነው፥ 20 ሚስቃል ወርቅ ደግሞ 4,25x 20 = 85 ግራም ወርቅ ይሆናል ማለት ነው። 
1 ሚስቃል ብር 2.975 ግራም ነው፥ 200 ሚስቃል ብር ደግሞ 2.975x 200= 595 ግራም ብር ይሆናል ማለት ነው።

በዘካህ ላይ የሚወጅበው ኒሷብ 85 ግራም ወርቅ ወይም 595 ግራም ብር ነው።
አንድ ሙሥሊም ያለው ካፒታል በዓመት ውስጥ 85 ግራም ወርቅ ወይም 595 ግራም ብር ያክል ከሆነ ዘካህ ማውጣት ግዴታው ነው። ይህ ኒሷብ ወደ ገንዘብ ለመቀየር ወርቅን ዛሬ ባለው በ 24 ካራት የወቅቱ ግብይት ለናሙና ያክል መሥራት ይቻላል፦
1. በስውዲን አንድ ግራም ወርቅ 396 ክራውን ነው፥ 396×85= 33,660 ክራውን ይሆናል። 
2. በኢትዮጵያ አንድ ግራም ወርቅ 1,181 ብር ነው፥ 1,181×85= 100,385 ብር ይሆናል።
3. በአሜሪካ አንድ ግራም ወርቅ 41.30 ዶላር ነው፥ 41.30×85= 3,510.30 ዶላር ይሆናል።

ስለዚህ አንድ ሙሥሊም ያለው ካፒታል በገንዘብ ሲተመን በስውዲን 33,660 ክራውን፣ በኢትዮጵያ 100,385 ብር፣ በአሜሪካ 3,510.30 ዶላር ወዘተ ከሆነ ከዚያ ወዲህ ዘካህ ማውጣቱ ፈርድ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በኢትዮ 100,385 ሺ ብር ካለው ከ 100,385 ሺ ብር ላይ 2.5% ዘካ ያወጣል፥ ያ ማለት የዘካው ብር 100,385×2.5÷100= ውጤቱ 2,509 ብር ይሆናል ማለት ነው። ዘካን የማይሰጥ በመጨረሻይቱ ዓለም ከአላህ ዘንድ መተሳሰብ የለም ብሎ የሚክድ ሰው ነው፦
41፥7 *”ለእነዚያ ዘካን ለማይሰጡት እነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም እነርሱ ከሓዲዎች ለኾኑት ወዮላቸው”*፡፡ الَّذِينَ لَا يُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَهُم بِالْآخِرَةِ هُمْ كَافِرُونَ 

አንድ ሙሥሊም ይህንን ዘካ ካላወጣ የትንሳኤ ቀን ገንዘቡ እንደ ሁለት አይኖቹ ላይ ጥቁር ነጥቦች የተጣሉበት ወንድ መላጣ እባብ ተመስሎ ይመጣና ማንገጭላውን አጥብቆ በመያዝ፦ “እኔ ገንዘብህ ነኝ፥ እኔ ድልብህ ነኝ” ይለዋል፦
3፥180 *”እነዚያም አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ገንዘብ የሚነፍጉ እርሱ ለእነርሱ ደግ አይምሰላቸው፡፡ ይልቁንም እርሱ ለእነርሱ መጥፎ ነው፡፡ ያንን በእርሱ የነፈጉበትን በትንሣኤ ቀን እባብ ኾኖ ይጠለቃሉ”*፡፡ የሰማያትና የምድርም ውርስ ለአላህ ብቻ ነው፡፡ አላህም በሚሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው፡፡ وَلَا يَحْسَبَنَّ الَّذِينَ يَبْخَلُونَ بِمَا آتَاهُمُ اللَّهُ مِن فَضْلِهِ هُوَ خَيْرًا لَّهُم ۖ بَلْ هُوَ شَرٌّ لَّهُمْ ۖ سَيُطَوَّقُونَ مَا بَخِلُوا بِهِ يَوْمَ الْقِيَامَةِ ۗ وَلِلَّهِ مِيرَاثُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۗ وَاللَّهُ بِمَا تَعْمَلُونَ خَبِيرٌ
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 90, ሐዲስ 5
አቢ ሁራይራ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ *”አላህ ገንዘብ ሰጥቶት የእሱን ዘካህ ያላወጣ የትንሳኤ ቀን ገንዘቡ እንደ ሁለት አይኖቹ ላይ ጥቁር ነጥቦች የተጣሉበት ወንድ መላጣ እባብ ተመስሎ ይመጣና ማንጋጭላውን አጥብቆ በመያዝ፦ “እኔ ገንዘብህ ነኝ፥ እኔ ድልብህ ነኝ ይለዋል”*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏”‏ يَكُونُ كَنْزُ أَحَدِكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ شُجَاعًا أَقْرَعَ، يَفِرُّ مِنْهُ صَاحِبُهُ فَيَطْلُبُهُ وَيَقُولُ أَنَا كَنْزُكَ‏.‏ قَالَ وَاللَّهِ لَنْ يَزَالَ يَطْلُبُهُ حَتَّى يَبْسُطَ يَدَهُ فَيُلْقِمَهَا فَاهُ

አላህ ከዚህ ቅጣት ይጠብቀን። የዘካህ ብር የሚውለው ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ ዘካን በማሰጠት ለሚያስተባብሩ፣ ልቦቻቸውም በኢሥላም ለሚለማመዱት፣ በባርነት ተገዢዎችን ነጻ ለማውጣት፣ ለባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም ለሚሠሩ፣ ለመንገደኛ ነው፦
9፥60 *ግዴታ ምጽዋቶች የሚከፈሉት ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም በኢሥላም ለሚለማመዱት፣ በባርነት ተገዢዎችን ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት”*፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡ إِنَّمَا الصَّدَقَاتُ لِلْفُقَرَاءِ وَالْمَسَاكِينِ وَالْعَامِلِينَ عَلَيْهَا وَالْمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمْ وَفِي الرِّقَابِ وَالْغَارِمِينَ وَفِي سَبِيلِ اللَّهِ وَابْنِ السَّبِيلِ ۖ فَرِيضَةً مِّنَ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌ

አምላካችን አላህ ሙንፊቂን ከሚላቸው ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

✍ከወንድም ወሒድ ዑመር